የማርቆስ ወንጌል 6:31-43

የማርቆስ ወንጌል 6:31-43 አማ05

እርሱም “እናንተ ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ወደ እነርሱ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ስለ ነበሩ ለመመገብ እንኳ ጊዜ ሊኖራቸው ስላልቻለ ነው። ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ፥ ሄዱ። ይሁን እንጂ እነርሱ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቁአቸው፤ ከየከተማውም ወጥተው በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸውና ወደ እነርሱ ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሰዎችን አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በመሆናቸውም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። ጊዜው እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ቦታው በረሓ ነው፤ ጊዜውም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙ እነዚህን ሰዎች አሰናብታቸው።” ኢየሱስ ግን፦ “የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ታዲያ፥ ሄደን የሚበሉትን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር ገዝተን እንስጣቸውን?” አሉ። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሂዱና እዩ፤” አላቸው፤ አይተውም “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አለ፤” አሉት። ኢየሱስም ሕዝቡን በቡድን ከፋፍለው፥ በለመለመው መስክ ላይ እንዲያስቀምጡአቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ስለዚህ ሕዝቡ በመቶና በኀምሳ ተከፋፍለው በቡድን ተቀመጡ። ኢየሱስም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እንዲሁም ሁለቱን ዓሣ ለሁሉም አከፋፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ። ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሰበሰቡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች