ማርቆስ 6:31-43
ማርቆስ 6:31-43 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው፤ ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው፤ ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፤ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ አሁንም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው፤” አሉት። እርሱ ግን መልሶ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። “ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ፤” አላቸው። ባወቁም ጊዜ “አምስት፥ ሁለትም ዓሣ፤” አሉት። ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከቍርስራሹም ዐሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ፤ ከዓሣውም ደግሞ።
ማርቆስ 6:31-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስኪ ብቻችሁን ከእኔ ጋራ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም ዐዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷል፤ በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” እርሱ ግን መልሶ፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስኪ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው። አይተውም፣ “ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ” አሉት። ከዚያም፣ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም መቶ መቶና ዐምሳ፣ ዐምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።
ማርቆስ 6:31-43 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። እርሱ ግን መልሶ፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። እርሱም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ፦ አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ።
ማርቆስ 6:31-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱም “እናንተ ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ወደ እነርሱ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ስለ ነበሩ ለመመገብ እንኳ ጊዜ ሊኖራቸው ስላልቻለ ነው። ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ፥ ሄዱ። ይሁን እንጂ እነርሱ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቁአቸው፤ ከየከተማውም ወጥተው በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸውና ወደ እነርሱ ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሰዎችን አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በመሆናቸውም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። ጊዜው እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ቦታው በረሓ ነው፤ ጊዜውም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙ እነዚህን ሰዎች አሰናብታቸው።” ኢየሱስ ግን፦ “የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ታዲያ፥ ሄደን የሚበሉትን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር ገዝተን እንስጣቸውን?” አሉ። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሂዱና እዩ፤” አላቸው፤ አይተውም “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አለ፤” አሉት። ኢየሱስም ሕዝቡን በቡድን ከፋፍለው፥ በለመለመው መስክ ላይ እንዲያስቀምጡአቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ስለዚህ ሕዝቡ በመቶና በኀምሳ ተከፋፍለው በቡድን ተቀመጡ። ኢየሱስም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እንዲሁም ሁለቱን ዓሣ ለሁሉም አከፋፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ። ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሰበሰቡ።
ማርቆስ 6:31-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፥ “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷአል፤ በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” እርሱ ግን መልሶ፥ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፥ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው። አይተውም፥ “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ።” ከዚያም፥ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም መቶ መቶና አምሳ አምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈላቸው። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከተበላው እንጀራና ዓሣ፥ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።