የማርቆስ ወንጌል 5:24-34

የማርቆስ ወንጌል 5:24-34 አማ05

ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት በዙሪያው ያጣብቡት ነበር። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች። ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ገንዘብዋንም ሁሉ ጨርሳ ነበር። ነገር ግን እየባሰባት ሄደ እንጂ ምንም አልተሻላትም። እርስዋም የኢየሱስን ዝና ሰምታ ስለ ነበር በሚጋፋው ሕዝብ መካከል ከበስተኋላው መጥታ ልብሱን ነካች። ይህንንም ያደረገችው፦ “ልብሱን እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” በሚል እምነት ነበረ። የሚፈሰው ደምዋም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሕመምዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ ተሰማት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፤ ወደ ሕዝቡም ዘወር ብሎ፦ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን?” አሉት። እርሱም ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዘወር ብሎ ተመለከተ። ሴትዮዋ ግን በእርስዋ የሆነውን በማወቅዋ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ወድቃ እውነቱን ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ፤” አላት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች