የማርቆስ ወንጌል 5:1-43

የማርቆስ ወንጌል 5:1-43 አማ05

የገሊላን ባሕር በጀልባ ተሻግረው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባው እንደ ወረደ አንድ በርኩስ መንፈስ የተያዘ ሰው ወዲያውኑ ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ተገናኘው። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ይኖር ነበር፤ ማንም በሰንሰለት እንኳ አስሮ ሊያቈየው አይችልም ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን ሰንሰለቱን እየበጣጠሰና እግር ብረቱንም እየሰባበረ ይጥል ነበር፤ ስለዚህ ይዞ ሊያቆመው የሚችል ማንም አልነበረም። ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን ባለማቋረጥ በየመቃብር ቦታና በየተራራው ላይ እየተዘዋወረ ይጮኽ ነበር፤ ሰውነቱን በድንጋይ እየቈራረጠ ያቈስል ነበር። እርሱም ኢየሱስን በሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጠና በጒልበቱ ተንበርክኮ ሰገደለት። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ፤ እባክህ አታሠቃየኝ!” አለው። ይህንንም ያለበት ምክንያት፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ አዞት ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም “ብዙዎች ስለ ሆንን ስሜ ሌጌዎን ነው፤” ሲል መለሰለት። ከዚያም አገር እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው። በዚያም ስፍራ በኮረብታዎች ጥግ ብዙ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ስለዚህ “እባክህ ሄደን ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን፤” ብለው ለመኑት፤ ኢየሱስም ፈቀደላቸው፤ ርኩሳን መናፍስቱም ከዚያ ሰው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ በመንጋዎቹ የነበሩት ሁለት ሺህ የሚያኽሉ ዐሣማዎች ከገደሉ በመንደርደር ወርደው በባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ። የዐሣማዎቹ እረኞች ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠር ወሬውን አወሩ፤ ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጡ፤ ወደ ኢየሱስም መጥተው ያ በርኩሳን መናፍስት ተይዞ የነበረው ሰው ከአእምሮው ሕመም ድኖ፥ ልብሱን ለብሶ፥ ተቀምጦም ባዩት ጊዜ ደነገጡ። ይህንንም ቀደም ብለው ያዩ ሰዎች ርኩስ መንፈስ ባደረበት ሰውና በዐሣማዎቹ የሆነውን ሁሉ አወሩላቸው። በዚያን ጊዜ የአገሩ ሰዎች ኢየሱስ ከአገራቸው ወጥቶ እንዲሄድላቸው ለመኑት። ኢየሱስ ወደ ጀልባው በመግባት ላይ ሳለ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው፦ “እባክህ ልከተልህ!” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፥ “ወደ ቤትህ ሂድና ጌታ ምን ያኽል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና እንዴትስ እንደማረህ ለቤተሰብህ አውራላቸው፤” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተሞች” በሚባል አገር ማውራት ጀመረ፤ የሰሙትም ሁሉ ይደነቁ ነበር። ኢየሱስ በጀልባ ወደ ባሕሩ ማዶ እንደገና በተመለሰ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በዚያ ጊዜ እርሱ በባሕሩ አጠገብ ነበር። እዚያም ከምኲራብ አለቆች አንዱ የነበረ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ሥር ወድቆ “ትንሽዋ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናት፤ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት!” ሲል አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት በዙሪያው ያጣብቡት ነበር። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች። ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ገንዘብዋንም ሁሉ ጨርሳ ነበር። ነገር ግን እየባሰባት ሄደ እንጂ ምንም አልተሻላትም። እርስዋም የኢየሱስን ዝና ሰምታ ስለ ነበር በሚጋፋው ሕዝብ መካከል ከበስተኋላው መጥታ ልብሱን ነካች። ይህንንም ያደረገችው፦ “ልብሱን እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” በሚል እምነት ነበረ። የሚፈሰው ደምዋም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሕመምዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ ተሰማት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፤ ወደ ሕዝቡም ዘወር ብሎ፦ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን?” አሉት። እርሱም ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዘወር ብሎ ተመለከተ። ሴትዮዋ ግን በእርስዋ የሆነውን በማወቅዋ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ወድቃ እውነቱን ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ፤” አላት። ኢየሱስ ገና ይህን በመናገር ላይ ሳለ ከምኲራብ አለቃው ቤት የመጡ ሰዎች የምኲራብ አለቃውን፦ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ ስለምን መምህሩን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ የምኲራቡን አለቃ፦ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ!” አለው። ኢየሱስ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ፥ ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር፥ ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሰዎቹ ሲንጫጩና ሲያለቅሱ፥ ሲጮኹም ተመለከተ። ወደ ውስጥ ገብቶም፦ “ይህ ሁሉ ሁካታና ለቅሶ ስለምንድን ነው? ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው። ሰዎቹም በማፌዝ ሳቁበት፤ ኢየሱስ ግን ሁሉንም ከቤት አስወጣ፤ የልጅትዋን አባትና እናት ከእርሱም ጋር የነበሩትን አስከትሎ፦ ልጅትዋ ወደነበረችበት ክፍል ገባ። የልጅትዋንም እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጒሙም “አንቺ ልጅ ተነሺ እልሻለሁ፤” ማለት ነው። እርስዋ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ስለ ነበረች ወዲያውኑ ተነሥታ ወዲያና ወዲህ ማለት ጀመረች፤ ይህም በሆነ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ተደነቁ። ኢየሱስ ግን ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አዘዛቸውና “የምትበላውን ስጡአት!” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች