ኢየሱስ እንደገና በባሕሩ አጠገብ ማስተማር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረው ጀልባ ገብቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። ብዙ ነገሮችንም በምሳሌ አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! እነሆ፥ ገበሬው ዘሩን ለመዝራት ወጣ፤ ሲዘራ ሳለ አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ቦታውም ብዙ ዐፈር ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ የጠለቀ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ባደገ ጊዜ ስላነቀው ያለ ፍሬ ቀረ። ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ኢየሱስ ብቻውን በሆነ ጊዜ ይከተሉት የነበሩ ሰዎችና ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ምሳሌዎቹ ትርጒም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጪ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል። ይህም የሚሆነው፥ ‘እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ኃጢአታቸው ይቅር እንዳይባልላቸው፥ ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤ መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’ ” በተባለው መሠረት ነው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም ይህ ምሳሌ አይገባችሁምን? ታዲያ፥ ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ዘሪው ቃልን ይዘራል፤ ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸውን ሰዎች ነው። እንዲሁም በጭንጫማ ቦታ ላይ የተዘራው የሚያመለክተው ቃሉን ሲሰሙ ወዲያው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ግን እነርሱ ለጊዜው ነው እንጂ በልባቸው ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቃሉ ምክንያት ችግር ወይም ስደት ቢደርስባቸው ወዲያውኑ ተሰናክለው ይወድቃሉ። በእሾኽ መካከል የተዘራው ደግሞ የሚያመለክተው ቃሉን የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብ፥ የሀብት ፍቅርና ሌላውም ከንቱ ምኞት ወደ ልባቸው ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት የተዘራው ግን የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በማስተዋል የሚቀበሉትን ሰዎች ነው። እንዲህ ዐይነቱ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ ፍሬ ያፈራል። “ሰው መብራትን አብርቶ በእንቅብ ውስጥ ወይም በአልጋ ሥር ያስቀምጠዋልን? የሚያስቀምጠው፥ ብርሃኑ በሚታይበት በመቅረዝ ላይ አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፤ በይበልጥም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ዘር የሚዘራውን ሰው ትመስላለች። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀንም ይነቃል፤ እንዴት እንደ ሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም። ምድሪቱም በገዛ ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፥ ቀጥሎም ዛላውን ታሳያለች፤ በኋላም በዛላው ፍሬ ይገኛል። ሰብሉም በደረሰ ጊዜ መከር በመሆኑ ሰውየው ወዲያውኑ ማጭድ ያዘጋጃል።” ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንገልጻታለን? የሰናፍጭን ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ ስትዘራ በምድር ላይ ካለው ዘር ሁሉ ያነሰች ናት። ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከአትክልት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በሥርዋ ጎጆ ሠርተው መጠለል እስኪችሉ ድረስ ታላላቅ ቅርንጫፎችን ታወጣለች።” ኢየሱስም ሰዎች ማስተዋል በሚችሉበት መጠን፥ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ቃሉን ይነግራቸው ነበር። ያለ ምሳሌም አያስተምራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን ሲሆኑ ግን ሁሉን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ያስረዳቸው ነበር።
የማርቆስ ወንጌል 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 4:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos