የማርቆስ ወንጌል 3:1-21

የማርቆስ ወንጌል 3:1-21 አማ05

ኢየሱስ እንደገና ወደ ምኲራብ ገባ፤ እዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበር። ኢየሱስን ሊከሱት የፈለጉ ሰዎች፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ!” ብለው ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም እጀ ሽባውን ሰው፦ “ና በመካከል ቁም” አለው። ከዚያም በኋላ “ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ። ኢየሱስም ስለ ልባቸው ድንዛዜ አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በቊጣ ተመለከተና ሰውየውን፦ “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። ወዲያውኑ ፈሪሳውያን ወጥተው እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያጠፉት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ተማከሩ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። ከገሊላና ከይሁዳ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። ያደርግ የነበረውንም ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እነርሱም ከገሊላ፥ ከይሁዳ፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር፥ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች የመጡ ነበሩ። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሰዎች እንዳያጣብቡት ጀልባ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ብዙ ሰዎችን ከበሽታ ፈውሷቸው ነበርና በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው፥ ያጨናንቁት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ሲያዩት በፊቱ እየተደፉ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ ይጮኹ ነበር። እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው። ኢየሱስ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እነዚያን የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡ። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ ለማስተማርም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡትም ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው ስምዖን፥ ቦአኔርጌስ ወይም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሠየማቸው፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ተቀናቃኙ ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውም አስቆሮታዊው ይሁዳ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤት ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። “ኢየሱስ አብዶአል” ሲባል በመስማታቸው ዘመዶቹ ሊይዙት ወደ እርሱ መጡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች