የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 3

3
ኢየሱስ እጀ ሽባውን ሰው ማዳኑ
(ማቴ. 12፥9-14ሉቃ. 6፥6-11)
1ኢየሱስ እንደገና ወደ ምኲራብ ገባ፤ እዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበር። 2ኢየሱስን ሊከሱት የፈለጉ ሰዎች፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ!” ብለው ይጠባበቁት ነበር። 3ኢየሱስም እጀ ሽባውን ሰው፦ “ና በመካከል ቁም” አለው። 4ከዚያም በኋላ “ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ። 5ኢየሱስም ስለ ልባቸው ድንዛዜ አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በቊጣ ተመለከተና ሰውየውን፦ “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። 6ወዲያውኑ ፈሪሳውያን ወጥተው እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያጠፉት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ተማከሩ።
ሕዝቡ በባሕሩ አጠገብ ወደ ኢየሱስ እንደ ተሰበሰቡ
7ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። ከገሊላና ከይሁዳ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። 8ያደርግ የነበረውንም ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እነርሱም ከገሊላ፥ ከይሁዳ፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር፥ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች የመጡ ነበሩ። 9ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሰዎች እንዳያጣብቡት ጀልባ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። #ማር. 4፥1፤ ሉቃ. 5፥1-3። 10ብዙ ሰዎችን ከበሽታ ፈውሷቸው ነበርና በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው፥ ያጨናንቁት ነበር። 11ርኩሳን መናፍስትም ሲያዩት በፊቱ እየተደፉ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ ይጮኹ ነበር።
12እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው።
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መምረጡ
(ማቴ. 10፥1-4ሉቃ. 6፥12-16)
13ኢየሱስ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እነዚያን የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡ። 14ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ ለማስተማርም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው። 15አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።
16የተመረጡትም ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው ስምዖን፥ 17ቦአኔርጌስ ወይም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሠየማቸው፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ 18እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ተቀናቃኙ ስምዖን፥ #3፥18 ተቀናቃኙ፦ ቀናኢ ማለት ነው፤ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባል ነው የሚሉም አሉ። 19ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውም አስቆሮታዊው ይሁዳ።
ኢየሱስና ብዔልዜቡል
(ማቴ. 12፥22-32ሉቃ. 11፥14-2312፥10)
20ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤት ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21“ኢየሱስ አብዶአል” ሲባል በመስማታቸው ዘመዶቹ ሊይዙት ወደ እርሱ መጡ።
22ከኢየሩሳሌም የወረዱ የሕግ መምህራን፥ “እርሱ ብዔልዜቡል አለበት! አጋንንትንም የሚያወጣው በዚሁ የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል አማካይነት ነው!” እያሉ አወሩ።
23ኢየሱስም እነርሱን ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? #ማቴ. 9፥34፤ 10፥25። 24አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በርሱ የሚጋጭ ከሆነ ያ መንግሥት ጸንቶ መቆም አይችልም። 25እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም፤ 26ስለዚህ ሰይጣን እርስ በርሱ ከተለያየ ይጠፋል እንጂ መኖር አይችልም።
27“እንዲሁም ወደ አንድ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ንብረቱን መዝረፍ የሚችል የለም።
28“በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች የሚሠሩት ኃጢአትና የሚናገሩት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል። 29ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘለዓለም ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ከቶ ኃጢአቱ ይቅር አይባልለትም።” #ሉቃ. 12፥10። 30ኢየሱስ ይህን የተናገረው፥ “ርኩስ መንፈስ አለበት፤” በማለታቸው ነበር።
የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ
(ማቴ. 12፥46-50ሉቃ. 8፥19-21)
31የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፤ በውጪም ቆመው ወደ እርሱ ሰው ላኩና አስጠሩት። 32በዙሪያውም ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች፥ “እነሆ! እናትህና ወንድሞችህ በውጪ ቆመው ይፈልጉሃል” ብለው ነገሩት።
33እርሱም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰ። 34በዙሪያው ተቀምጠው ወደነበሩት እየተመለከተ፥ “እነሆ! እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! 35የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜም፥ እኅቴም እናቴም ነው።” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማርቆስ ወንጌል 3