የማርቆስ ወንጌል 15:21-32

የማርቆስ ወንጌል 15:21-32 አማ05

ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም። ከዚህም በኋላ ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት። ኢየሱስን ሲሰቅሉት ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። ወንጀሉንም ለማመልከት “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር። ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። [ በዚህም ሁኔታ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጸመ።] በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር፦ “አዬ፥ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” በዚህ ዐይነት የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራንም እርስ በርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ይዘባበቱበት ነበር፦ “ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንይና እንመንበት!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች