ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሸንጎውም አባሎች ሁሉ ጋር ተማከሩ፤ ከዚያም በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው፤” አለው። የካህናት አለቆች ግን ኢየሱስን በብዙ ይወነጅሉት ነበር። ስለዚህ ጲላጦስ “በስንት ነገር እንደሚከሱህ ተመልከት! ከቶ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ አሁንም ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም። ጲላጦስ በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሰዎቹ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ይለቅላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በመንግሥት ላይ ተነሣሥተው፥ ሰው በመግደል ወህኒ ቤት የገቡ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከነዚህም ዐመፀኞች አንዱ በርባን የሚባለው ሰው ነበር። ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። እርሱም “የአይሁድን ንጉሥ ፈትቼ እንድለቅላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። ይህንንም ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው። የካህናት አለቆች ግን፥ “በእርሱ ፈንታ በርባን ይፈታልን፤” ብለው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሰዎቹን አነሣሡ። ጲላጦስም፦ “ታዲያ፥ ይህን የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላድርገው?” ሲል ሰዎቹን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ እንደገና ጮኹ። ጲላጦስም “ለምን? ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ የቀሩትንም ወታደሮች ሁሉ ጠሩ፤ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበትና፤ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ በማፌዝ እጅ ይነሡት ነበር። በመቃ ራስ ራሱን ይመቱት ነበር፤ ምራቃቸውንም እንትፍ ይሉበት ነበር፤ በፊቱም በማላገጥ እየተንበረከኩ ይሰግዱለት ነበር። ካፌዙበትም በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው፥ የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም።
የማርቆስ ወንጌል 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 15:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos