የማርቆስ ወንጌል 14:53-61

የማርቆስ ወንጌል 14:53-61 አማ05

ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው።