የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 14:32-50

የማርቆስ ወንጌል 14:32-50 አማ05

ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።” ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ ጴጥሮስን፦ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ ልትነቃ አልቻልክምን?” አለው። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አላቸው። እንደገናም ሄዶ፥ ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ጸለየ። ደግሞም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር፥ ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛም ጊዜ ወደ እነርሱ መጥቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እንግዲህስ በቃ! ሰዓቱ ደርሶአል! እነሆ! የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። በሉ ተነሡ! እንሂድ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቦአል!” ወዲያውም ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ የተላኩ ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ፥ “እናንተ የምትይዙት እኔ ሰላምታ ሰጥቼ የምስመውን ነው፤ እርሱን በጥንቃቄ ይዛችሁ ውሰዱት፤” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ያዙት። እዚያ ቆመው ከነበሩት ከኢየሱስ ተከታዮች አንዱ ሰይፉን መዝዞ የካህናት አለቃውን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን እንደ ወንበዴ ለመያዝ ነውን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዲፈጸም ነው።” ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ።