እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።” ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ ‘እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ፤’ ተብሎ ተጽፎአልና ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፤ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ትታችሁኝም ትሸሻላችሁ፤ ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ፥ እኔ ከቶ አልክድህም!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “መሞት እንኳ ቢያስፈልግ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” እያለ አጠንክሮ ተናገረ። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።”
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:22-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች