ማርቆስ 14:22-36

ማርቆስ 14:22-36 NASV

ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ’ ከተነሣሁ በኋላ ግን፣ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለ። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋራ ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ከርሱ ጋራ ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ ቢቻል ሰዓቱ ከርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፣ “አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ።