ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን በምሳሌ እንዲህ ሲል ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ዙሪያውንም ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ከፍተኛ የግንብ ማማ ሠራ፤ ከዚህም በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ፍሬው በደረሰ ጊዜ፥ ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት አገልጋዩን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ይዘው ከደበደቡት በኋላ ባዶ እጁን ሰደዱት። እንደገና ባለቤቱ ሌላ አገልጋይ ላከ፤ ገበሬዎቹ ይህንንም በድንጋይ ፈንክተውና አዋርደው ሰደዱት። ቀጥሎም ሌላውን ቢልክ ገደሉት፤ እንዲሁም ብዙዎችን ቢልክ፥ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ ሌሎቹንም ገደሉ። አሁን ማድረግ የቀረው የሚወደውን ልጁን መላክ ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ‘ልጄንስ ያከብሩት ይሆናል’ ብሎ በማሰብ በመጨረሻ አንድ ልጁን ላከ። ነገር ግን ገበሬዎቹ እርስ በርሳቸው ‘ይህማ ወራሹ ነው! ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። ስለዚህ ልጁን ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ተክልም ቦታ ውጪ ጣሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ ምን ያደርጋል? ባለቤቱ ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም ተክል ለሌሎች ይሰጣል። ለመሆኑ፥ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ይህም የጌታ ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።’ ” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን? የአይሁድ አለቆች ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ እነርሱን የሚመለከት መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈርተው ትተውት ሄዱ። ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በንግግሩ ለማጥመድ ወደ እርሱ ተላኩ። ቀርበውም እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራትና በይሉኝታ የምታደርገው ነገር የለም፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት ታስተምራለህ፤ ታዲያ፥ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን? ወይስ አይደለም? እንገብር ወይስ አንገብር?” ኢየሱስም ግብዝነታቸውን ዐውቆ፦ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ ገንዘቡን አምጡና አሳዩኝ፤” አላቸው። እነርሱም ገንዘቡን አመጡለት፤ እርሱም “በዚህ ገንዘብ ላይ ያለው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው፤” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም በመልሱ ተደነቁ። “የሙታን መነሣት የለም፤” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው፤ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፥ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ፥ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም ወንድሙ ያቺኑ ሴት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ ሆነ፤ በዚህ ሁኔታ ሰባቱም አግብተዋት ዘር ሳይተኩ ሞቱ፤ ከሁሉም በኋላ ደግሞ ሴትዮዋ ሞተች። ሰባቱም ወንድማማች በየተራ አግብተዋታልና እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ አይደለምን? ሙታንስ ሲነሡ በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን መነሣት የሆነ እንደ ሆነ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ከቊጥቋጦው እሳት ውስጥ ምን እንደ ተናገረው ከሙሴ መጽሐፍ አላነበባችሁምን? ይኸውም ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ያለው ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ እናንተ ግን እጅግ ትሳሳታላችሁ።” ከሕግ መምህራን አንዱ ክርክራቸውን ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ በመልካም ሁኔታ እንደ መለሰላቸው የሕግ መምህሩ አስተዋለ፤ ወደ ኢየሱስ ቀርቦም “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ፥ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ አምላክ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ይህንንም የሚመስል ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ከነዚህም ከሁለቱ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” የሕግ መምህሩም ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “መምህር ሆይ! ‘እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለህ የተናገርከው ልክ ነው፤ ስለዚህ ሰው በፍጹም ልቡ፥ [በፍጹም ነፍሱ፥] በፍጹም ሐሳቡ፥ በፍጹም ኀይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል፤ እንዲሁም ጐረቤትን እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ ይገባዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ እነዚህን ሁለቱን ትእዛዞች መጠበቅ ይበልጣል።” ኢየሱስም የሕግ መምህሩ በጥበብና በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ፥ “አንተስ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህ በኋላ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤ “የሕግ መምህራን ‘መሲሕ የዳዊት ልጅ ነው፤’ ስለምን ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ፥ ‘እግዚአብሔር ለጌታዬ (ለመሲሑ)፥ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤’ ብሎታል። ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ኢየሱስ ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ለማግኘት ይመርጣሉ። ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ቤት ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱ የባሰ ፍርድ ይደርስባቸዋል።” ኢየሱስ በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ፊት ለፊት ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ ያይ ነበር፤ ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በዚያ ውስጥ ጨመረች። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሰዎች ሁሉ አብልጣ የጨመረች ይህች ድኻ መበለት ናት። ሌሎቹ ሁሉ የሰጡት ካላቸው ሀብት የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”
የማርቆስ ወንጌል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 12:1-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos