በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ክፍለ ሀገር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ዮሐንስም ወዲያውኑ ኢየሱስ ከውሃው እንደ ወጣ ሰማይ ሲከፈትና መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ። በዚያን ጊዜ፥ “በአንተ ደስ የሚለኝ፥ የምወድህ ልጄ ነህ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ኢየሱስን ወደ በረሓ ወሰደው። በዚያም በረሓ በሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ቈየ፤ ከአራዊትም ጋር ነበረ፤ መላእክትም አገለገሉት። ዮሐንስም ተይዞ ወደ እስር ቤት ከገባ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። ሲያስተምርም፦ “ዘመኑ ተፈጽሞአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ! በወንጌልም እመኑ!” ይል ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፦ “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችንም እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት አለፍ እንዳለ፥ ሌሎች ሁለት ወንድማማችን አየ፤ እነርሱም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ፤ እነርሱ በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ ነበር፤ ኢየሱስ ወዲያውኑ ጠራቸው፤ እነርሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከሠራተኞቹ ጋር በጀልባው ላይ ትተውት ኢየሱስን ተከተሉት። አልፈውም ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ደረሱ፤ ወዲያው በሚቀጥለውም ሰንበት ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ፥ የሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዐይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበት በምኲራባቸው የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።” ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ “ጸጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ። “ይህ ምንድን ነው? ምን ዐይነት አዲስ ትምህርት ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ በሥልጣኑ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤” እያሉ ሁሉም በመገረም እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:9-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች