በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ከምኲራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ገባ። በቤት ውስጥ፥ የስምዖን ዐማት በንዳድ ሕመም አተኲሶአት ተኝታ ነበር፤ ስለ እርስዋም መታመም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀረበና እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ትኲሳቱም ወዲያው ለቀቃት፤ ተነሥታም አስተናገደቻቸው። ፀሐይ ጠልቃ በመሸ ጊዜ ሰዎች በሽተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ። የከተማው ሰዎች ሁሉ በደጅ ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስ በልዩ ልዩ በሽታ የሚሠቃዩትን ብዙ ሰዎች ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትንም አስወጣ፤ አጋንንቱም እርሱ ማን እንደ ሆነ ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ሊነጋ ሲል፥ ኢየሱስ በማለዳ ተነሥቶ ወጣና ለመጸለይ ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እርሱን ፍለጋ ወጥተው ሄዱ። ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዎች ሁሉ ይፈልጉሃል” አሉት። ኢየሱስም፦ “እኔ የመጣሁት ለማስተማር ስለ ሆነ ወንጌልን እንዳስተምር በቅርብ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ!” አላቸው። ስለዚህ በየምኲራቦቻቸው እያስተማረና አጋንንትን እያስወጣ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። አንድ ለምጻም ወደ ኢየሱስ መጣና በእግሩ ሥር ተንበርክኮ፦ “ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ሲል ለመነው። ኢየሱስም ራራለትና እጁን ዘርግቶ እየዳሰሰው፥ “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ኢየሱስ ሰውዬውን በጥብቅ አስጠንቅቆ አሰናበተው፤ “ይህን ነገር ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለሕዝቡም ምስክር እንዲሆን ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ፤” ብሎ አዘዘው። ይሁን እንጂ ሰውየው ከዚያ ወጥቶ ይህን ነገር ለሰው ሁሉ ማውራት ጀመረ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማናቸውም ከተማ በግልጥ መግባት አልቻለም። ነገር ግን ከከተማ ውጪ ሰው በሌለበት ቦታ ይኖር ነበር፤ ሆኖም ሰዎች ከየስፍራው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:29-45
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች