ይህ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ ነው፤ በነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ አስቀድሜ እልካለሁ፤ ይህም፦ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ’ እያለ፥ በበረሓ ከፍ አድርጎ የሚናገር ሰው ድምፅ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ “የኃጢአትን ይቅርታ እንድታገኙ፥ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ” በማለት በበረሓ እያወጀ መጣ። ከይሁዳ ምድርና ከኢየሩሳሌም ከተማ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጒር የተሠራ ነበር፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር. ነበር። እንዲህም ይል ነበር፦ “የጫማውን ማሰሪያ ጐንበስ ብዬ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ እጅግ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ክፍለ ሀገር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ዮሐንስም ወዲያውኑ ኢየሱስ ከውሃው እንደ ወጣ ሰማይ ሲከፈትና መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ። በዚያን ጊዜ፥ “በአንተ ደስ የሚለኝ፥ የምወድህ ልጄ ነህ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ኢየሱስን ወደ በረሓ ወሰደው። በዚያም በረሓ በሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ቈየ፤ ከአራዊትም ጋር ነበረ፤ መላእክትም አገለገሉት። ዮሐንስም ተይዞ ወደ እስር ቤት ከገባ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። ሲያስተምርም፦ “ዘመኑ ተፈጽሞአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ! በወንጌልም እመኑ!” ይል ነበር።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos