ትንቢተ ሚክያስ 5
5
ከቤተልሔም መሪ የሚወጣ ስለ መሆኑ የተነገረ ትንቢት
1“አንቺ የወታደር ከተማ ሠራዊትሽን አሰልፊ! ከበባው በእኛ ላይ ተጠናክሮአል፤ የእስራኤልንም መሪ ጒንጩ ላይ በበትር ይመቱታል።”
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አንቺ በኤፍራታ ምድር የምትገኚ ቤተልሔም ሆይ! ከይሁዳ ትናንሽ ከተሞች አንድ ብትሆኚም እንኳ ከአንቺ አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ የእስራኤልን ሕዝብ የሚመራ ገዢ ይወጣልኛል።” #ማቴ. 2፥6፤ ዮሐ. 7፥42።
3ስለዚህ እናቱ እርሱን እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይተዋቸዋል፤ ከዚህ በኋላ በስደት ላይ ያሉት ወገኖቹ ተመልሰው ከወገኖቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ። 4እርሱ በእግዚአብሔር ኀይል ተነሥቶ የበግ መንጋውን ያሰማራል፤ ይህንንም የሚያደርገው በግርማዊው በእግዚአብሔር በአምላኩ ስም ነው፤ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ስለሚሆን እነርሱ ያለ ስጋት ይኖራሉ። 5እርሱም ሰላማቸው ይሆናል። አሦራውያን ምድራችንን ለመውረር ቢመጡና በምሽጎቻችን ላይ ቢወጡ ሰባት ጠባቂዎችንና ስምንት መሪዎችን በእነርሱ ላይ እናስነሣለን። #5፥5 ምሽጎቻችን፦ በዕብራይስጥ “ምሽጎቻችን” የሚል ሲሆን አንዳንድ የጥንት ትርጒሞች “ምድራችን” ይላሉ። 6የናምሩድ ግዛት የነበረችውንም በሠራዊታቸው ኀይል አሦርን ድል ነሥተው ይይዛሉ፤ አሦራውያን አገራችንን ቢወሩና ድንበራችንን ቢረግጡ እርሱ ከእጃቸው ያድነናል። #ዘፍ. 10፥8-11።
7ከሞት የተረፉትም የእስራኤል ሕዝብ በብዙ ሕዝቦች መካከል እግዚአብሔር እንደሚልከው ጠልና በሣር እንደሚወርድ ካፊያ ይሆናሉ፤ ተማምነው የሚጠባበቁት ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ብቻ ይሆናል። 8አንበሳ በብዙ የዱር አራዊት መካከል፥ የአንበሳ ደቦልም በበግ መንጋዎች መካከል ዘለው ጉብ እያሉባቸውና እየቦጫጨቁ በሚሄዱበት ጊዜ ለአራዊቱ ምንም ረዳት አይገኝላቸውም፤ ከሞት የተረፉትንም የያዕቆብን ልጆች በብዙ ሕዝቦች መካከል እንደዚሁ ያደርጋሉ። 9የእስራኤል ኀይል በጠላቶቹ ላይ ይነሣል፤ ጠላቶቹም ሁሉ ይጠፋሉ።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቀደም ብዬ ግን ፈረሶቻችሁን ከመካከላችሁ አጠፋለሁ፤ ሠረገሎቻችሁንም እደመስሳለሁ። 11በምድራችሁ የሚገኙትን ከተሞች አጠፋለሁ፤ ምሽጎቻችሁንም ሁሉ አፈራርሳለሁ፤ 12መተታችሁን አጠፋለሁ፤ ሟርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ በመካከላችሁ አይገኙም። 13የተቀረጹ ጣዖቶቻችሁንና የምትሰግዱላቸው ዐምዶቻችሁን ከመካከላችሁ አጠፋለሁ፤ የእጆቻችሁ ሥራ ለሆኑ ጣዖቶች ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግዱም። 14የአሼራን ምስል ከምድራችሁ እነቃቅላለሁ፤ ከተሞቻችሁንም አፈራርሳለሁ። 15ለእኔ አልታዘዝም ያሉትን መንግሥታት ሁሉ በታላቅ ቊጣዬ እበቀላቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997