ትንቢተ ሚክያስ 1
1
በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚሆን የለቅሶ ዋይታ
1ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ በተከታታይ በይሁዳ በነገሡበት ዘመን እግዚአብሔር ለሞሬታዊው ለሚክያስ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም በራእይ በገለጠለት ጊዜ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
2እናንተ ሕዝቦች ሁላችሁም ይህን ስሙ!
በምድር ላይ የምትኖሩ ሁሉ ይህን አድምጡ!
ጌታ እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ ሆኖ ያጋልጣችኋል።
3እነሆ፥ እግዚአብሔር ከቦታው ወጥቶ ይመጣል፤
ወርዶም በምድር ከፍታ ቦታዎች ላይ ይራመዳል።
4በዚያን ጊዜ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥና፥
ውሃም ከከፍተኛ ቦታ ወደ ታች እንደሚወርድ
እንዲሁም ተራራዎች ከእርሱ ሥር ይቀልጣሉ፤
ሸለቆዎችም ይከፈታሉ።
5ይህ ሁሉ የሆነው እስራኤላውያን በፈጸሙት በደል ምክንያት ነው፤ የእስራኤል ሕዝብ እንዲያምፁ ምክንያት የሆነው ማን ነው? ዋና ከተማዋ ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ ሕዝብ ጣዖት በማምለክ ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገ ማን ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? 6ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ሰማርያን በሜዳ ላይ እንደሚታይ የቤት ፍርስራሽ ክምር አደርጋለሁ፤ የወይን መትከያ ቦታ ትሆናለች፤ የከተማይቱንም ፍርስራሽ ድንጋይ ወደ ሸለቆ አፈሰዋለሁ፤ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ። 7ምስሎችዋ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ ለመቅደስዋ አመንዝሮች የተከፈለውም ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ፤ ጣዖቶችዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ ሰማርያ እነዚህን ምስሎች የሰበሰበቻቸው የዝሙት ዋጋ መቀበያ ለማድረግ ነበር፤ አሁንም ጠላቶችዋ የዝሙት መጠቀሚያ ያደርጉአቸዋል።”
በይሁዳ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት
8ከዚህ በኋላ ሚክያስ እንዲህ አለ፦ “በዚህ ምክንያት ‘ዋይ! ዋይ!’ እያልኩ አለቅሳለሁ፤ ሐዘኔንም ለመግለጥ ራቊቴንና ባዶ እግሬን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ እጮኻለሁ፤ እንደ ሰጎንም የዋይታ ድምፅ አሰማለሁ። 9የሰማርያ ቊስል ሊፈወስ የሚችል አይደለም፤ ይህም ሥቃይ ወደ ይሁዳ ደርሶአል፤ ሕዝቤ ወደሚሰበሰቡበት ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይም ተዛምቶአል።”
10በጌት ላሉት ጠላቶቻችን የደረሰብንን መከራ አትንገሩአቸው፤ በዚያም ፈጽሞ አታልቅሱ፤ በቤትዖፍራ በሚገኙት ወገኖቻችን መካከል ግን በትቢያ ላይ እየተንከባለላችሁ አልቅሱ! 11እናንተ የሻፊር ሕዝቦች ራቊታችሁን ምርኮኞች ሆናችሁ በዕፍረት ዕለፉ፤ የጻእናን ኗሪዎች ከከተማው ለመውጣት አይደፍሩም፤ ቤትኤጼል ራስዋ የለቅሶ ቦታ ስለ ሆነች ለእናንተ መጠጊያ ልትሆን አትችልም። 12የማሮት ሕዝብ “መልካም ነገር ይመጣልናል” ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ግን ጥፋትን በኢየሩሳሌም ላይ አውርዶአል። 13የእስራኤል በደል በእናንተ ስለ ተገኘና ለኢየሩሳሌም የኃጢአት መጀመሪያ ስለ ሆናችሁ የላኪሽ ነዋሪዎች ሆይ፥ የሠረገላውን ፈረሶች ለጒሙ። 14የይሁዳ ሕዝብ ሆይ፥ እናንተ እንግዲህ ለሞሬሼት ጋት የመሰነባበቻ ስጦታ ትሰጣላችሁ፤ የአክዚብም ሕዝብ የእስራኤልን ነገሥታት ያታልላሉ።
15የመሪሳ ሕዝብ ሆይ! ወራሪ ጠላት አመጣባችኋለሁ፤ የተከበሩ የእስራኤል መሪዎችም በዐዱላም ዋሻ ይሸሸጋሉ። 16እናንተ የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ልጆቻችሁ ተማርከው ስለሚወሰዱ፥ ስለ ነዚህ ስለምትወዱአቸው ልጆቻችሁ ሐዘን ጠጒራችሁን ተላጩ፤ ራሳችሁም እንደ ጥንብ አንሣ ራስ መላጣ ይሁን።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997