የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 7:13-29

የማቴዎስ ወንጌል 7:13-29 አማ05

“በጠባብዋ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚያስገባው በር ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነው። ወደዚያ የሚገቡትም ሰዎች ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ ነው፤ መንገዱም አስቸጋሪ ነው፤ እርሱን የሚያገኙት ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፥ በውስጣቸው ግን እንደ ነጣቂ ተኲላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም የምታውቁአቸው በሥራቸው ፍሬ ነው። ከእሾኽ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ፥ ከኮሸሽላስ የበለስ ፍሬ ይለቀማልን? እንዲሁም መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ መጥፎ ዛፍም መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ፥ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል። ስለዚህ፥ ሐሰተኞች ነቢያትን በሥራቸው ፍሬ ታውቁአቸዋላችሁ። ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚገባው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። በፍርድ ቀን ብዙዎች፥ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። እኔም በዚያ ቀን፥ ‘በጭራሽ አላውቃችሁም! እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ!’ እላቸዋለሁ። “ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውለው ሁሉ፥ ቤቱን በድንጋይ መሠረት ላይ የሠራ ብልኅ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍ ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያን ቤት ገፋው፤ ይሁን እንጂ፥ ቤቱ በድንጋይ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ግን፥ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሞኝ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍም ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያንን ቤት ገፋው፤ ቤቱም ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ባበቃ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። የተደነቁትም እርሱ እንደ ሕግ መምህሮቻቸው ሳይሆን፥ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች