“መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች በመንፈሳዊ ኑሮአቸው ድኾች መሆናቸው የሚሰማቸው የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር መጽናናትን ስለሚሰጣቸው የሚያዝኑ የተባረኩ ናቸው። ትሑቶች ምድርን ስለሚወርሱ የተባረኩ ናቸው። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ስለሚጠግቡ የተባረኩ ናቸው። ምሕረትን ስለሚያገኙ ምሕረትን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔርን ስለሚያዩት ንጹሕ ልብ ያላቸው የተባረኩ ናቸው። በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች የተባረኩ ናቸው። “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ፥ በውሸትም ስማችሁን ሲያጠፉት ደስ ይበላችሁ። በመንግሥተ ሰማይ የምታገኙት ዋጋ ትልቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ ስደትና መከራ አድርሰውባቸዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እንደ ምድር ጨው ናችሁ፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ እንዴት ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ወደ ውጪ ከመጣልና በሰው እግር ከመረገጥ በቀር ወደፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ሰዎች መብራት አብርተው በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በከፍተኛ ቦታ ያስቀምጡታል እንጂ ከእንቅብ በታች አያኖሩትም። እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት፥ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የኦሪትን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ እንዲፈጸሙ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ አትሻርም። ስለዚህ ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛ የሆነችውን አንድዋን እንኳ የሚያፈርስና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ትእዛዞችን ሁሉ የሚፈጽምና ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲፈጽሙ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። ስለዚህ የእናንተ ጽድቅ ከሕግ መምህራንና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ።
የማቴዎስ ወንጌል 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 5:3-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች