የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 5:1-48

የማቴዎስ ወንጌል 5:1-48 አማ05

ኢየሱስ የሚከተለውን ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ፥ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀረቡ። እንዲህ እያለም ያስተምራቸው ጀመር፤ “መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች በመንፈሳዊ ኑሮአቸው ድኾች መሆናቸው የሚሰማቸው የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር መጽናናትን ስለሚሰጣቸው የሚያዝኑ የተባረኩ ናቸው። ትሑቶች ምድርን ስለሚወርሱ የተባረኩ ናቸው። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ስለሚጠግቡ የተባረኩ ናቸው። ምሕረትን ስለሚያገኙ ምሕረትን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔርን ስለሚያዩት ንጹሕ ልብ ያላቸው የተባረኩ ናቸው። በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች የተባረኩ ናቸው። “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ፥ በውሸትም ስማችሁን ሲያጠፉት ደስ ይበላችሁ። በመንግሥተ ሰማይ የምታገኙት ዋጋ ትልቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ ስደትና መከራ አድርሰውባቸዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እንደ ምድር ጨው ናችሁ፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ እንዴት ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ወደ ውጪ ከመጣልና በሰው እግር ከመረገጥ በቀር ወደፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ሰዎች መብራት አብርተው በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በከፍተኛ ቦታ ያስቀምጡታል እንጂ ከእንቅብ በታች አያኖሩትም። እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት፥ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የኦሪትን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ እንዲፈጸሙ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ አትሻርም። ስለዚህ ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛ የሆነችውን አንድዋን እንኳ የሚያፈርስና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ትእዛዞችን ሁሉ የሚፈጽምና ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲፈጽሙ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። ስለዚህ የእናንተ ጽድቅ ከሕግ መምህራንና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ። “በቀድሞ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የተባለውን ሰምታችኋል፤ ይኸውም ‘አትግደል፤ ሰውን የገደለ ይፈረድበታል’ የሚል ነው። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ፤ ክፉ ለሚያደርጉባችሁና ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ” እላችኋለሁ። ይህን ብታደርጉ፥ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣል፤ እንዲሁም ለጻድቃንና ለግፈኞች ዝናቡን ያዘንባል። የሚወዱአችሁን ሰዎች ብቻ ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ኃጢአተኞችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ለወንድሞቻችሁ ብቻ ሰላምታ የምትሰጡ ከሆነ ምን ብልጫ ያለው ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹሞች ሁኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች