የማቴዎስ ወንጌል 4:12-22

የማቴዎስ ወንጌል 4:12-22 አማ05

ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፥ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ መጥቶ ኖረ። ይህም የሆነው፥ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው የትንቢት ቃል እንዲፈጸም ነው፤ “ወደ ባሕሩ በሚወስደው መንገድና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የሚገኙት የዛብሎን ምድር፥ የንፍታሌም ምድር፥ የአሕዛብም ገሊላ፥ በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ የሞት ጥላ በጣለበት ምድር ለሚኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ!” እያለ መስበክ ጀመረ። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ዓሣ አጥማጆች የነበሩትን ሁለት ወንድማማች እነርሱም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን፥ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችን እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ፥ የዘብዴዎስ ልጆች የሆኑትን ሌሎች ሁለት ወንድማማች ያዕቆብንና ዮሐንስን አየ። እነርሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ሲጠግኑ ሳለ ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች