ከዚህ በኋላ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ከመቃብሩ በፍጥነት ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። ኢየሱስ በመንገድ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡና እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ የሚያዩኝም በዚያ ነው” አላቸው። ሴቶቹም ሲሄዱ ሳሉ ከወታደሮቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸውና እንዲህ አሉአቸው፤ “ ‘እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰርቀው ይዘውት ሄዱ’ ብላችሁ ለሕዝቡ ንገሩ። ይህን አገር ገዢው የሰማ እንደ ሆነ እኛ ጉዳዩን ለእርሱ አስረድተን በማሳመን በእናንተ ላይ ችግር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን። ” ስለዚህ ወታደሮቹ ገንዘቡን ተቀብለው ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ይህም ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ተስፋፍቶ ይነገራል። ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ እንዲሄዱ ወደ አመለከታቸው፥ በገሊላ ወደሚገኘው ተራራ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ አንዳዶቹ ግን ተጠራጠሩ፤ ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበና እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው። ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ አስተምሩአቸው! እነሆ፥ እኔም እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
የማቴዎስ ወንጌል 28 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 28:8-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos