ሴቶቹም በፍርሀትና በደስታ ተሞልተው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በፍጥነት እየሮጡ የመቃብሩን ስፍራ ትተው ሄዱ። ወዲያው ኢየሱስ አገኛቸውና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት። ኢየሱስም፣ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” አላቸው። ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ከጠባቂዎቹ ጥቂቶቹ ወደ ከተማ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩላቸው። የካህናት አለቆችም ከሽማግሌዎች ጋራ ተሰብስበው ተማከሩ፤ ለወታደሮቹ በቂ ገንዘብ በመስጠት እንዲህ አሏቸው፤ “ ‘ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ፤ ይህ ወሬ በገዥው ዘንድ ቢሰማ እንኳ፣ እኛ እናስረዳዋለን፤ ምንም ክፉ ነገር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን።” ወታደሮቹም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ ታዘዙት አደረጉ። ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዶች ዘንድ በሰፊው እንደ ተሠራጨ ነው። ከዚያም ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህም አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ።”
ማቴዎስ 28 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 28
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 28:8-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos