ሰንበት ካለፈ በኋላ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት፥ በማለዳ መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም መቃብሩን ለማየት ሄዱ። እነሆ፥ በድንገት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የጌታ መልአክ ከሰማይ ወርዶ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ አንከባለለና በላዩ ተቀመጠ። የመልአኩ ፊት እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሣ በመንቀጥቀጥ እንደ በድን ሆኑ፤ መልአኩ ግን ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ ዐውቃለሁ፤ እርሱ እዚህ የለም ቀደም ብሎ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል። እዚህ የለም፤ ተቀብሮበት የነበረበትን ስፍራ ኑና እዩ። እንግዲህ በፍጥነት ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ‘ከሞት ተነሥቶአል! እነሆ፥ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያ ታገኙታላችሁ!’ ብላችሁ ንገሩአቸው፤ እነሆ፥ ነግሬአችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ከመቃብሩ በፍጥነት ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። ኢየሱስ በመንገድ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡና እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ የሚያዩኝም በዚያ ነው” አላቸው። ሴቶቹም ሲሄዱ ሳሉ ከወታደሮቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸውና እንዲህ አሉአቸው፤ “ ‘እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰርቀው ይዘውት ሄዱ’ ብላችሁ ለሕዝቡ ንገሩ። ይህን አገር ገዢው የሰማ እንደ ሆነ እኛ ጉዳዩን ለእርሱ አስረድተን በማሳመን በእናንተ ላይ ችግር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን። ” ስለዚህ ወታደሮቹ ገንዘቡን ተቀብለው ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ይህም ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ተስፋፍቶ ይነገራል።
የማቴዎስ ወንጌል 28 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 28:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos