የማቴዎስ ወንጌል 27:45-66

የማቴዎስ ወንጌል 27:45-66 አማ05

ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ። በሩቅ ሆነው የሚመለከቱት ብዙ ሴቶችም በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ ከገሊላ ጀምረው ኢየሱስን እያገለገሉ ይከተሉት የነበሩ ናቸው። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙባቸው ነበር። በመሸ ጊዜ ዮሴፍ የሚባል አንድ የአርማትያስ ከተማ ሀብታም ሰው ወደዚያ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ ይህ ሰው፥ ወደ ጲላጦስ ሄደና የኢየሱስን አስከሬን ለመነ፤ ጲላጦስም አስከሬኑ እንዲሰጠው አዘዘ። ስለዚህ ዮሴፍ አስከሬኑን አውርዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው። ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ከዚህ በኋላ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘጋና ሄደ። መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም፥ እዚያ በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር። በማግስቱ ቅዳሜ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን በአንድነት ወደ ጲላጦስ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ “ጌታ ሆይ! ያ አሳሳች ገና በሕይወቱ ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት እነሣለሁ’ ያለው ትዝ አለን። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡም ‘እነሆ፥ ከሞት ተነሥቶአል’ እንዳይሉ መቃብሩ እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ አለበለዚያ የኋለኛው ማሳሳት ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።” ጲላጦስም “እነሆ፥ የሚጠብቁ ወታደሮች አሉአችሁ፤ ሂዱና በምታውቁት ዐይነት አስጠብቁ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው ድንጋዩን በማኅተም አሸጉና መቃብሩን በወታደሮች አስጠበቁ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች