የማቴዎስ ወንጌል 26:26-35

የማቴዎስ ወንጌል 26:26-35 አማ05

ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች