ማቴዎስ 26:26-35

ማቴዎስ 26:26-35 NASV

እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋራ መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች