የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 25:31-45

የማቴዎስ ወንጌል 25:31-45 አማ05

“የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ በክብር ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እርሱም ሕዝቦችን እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል። ጻድቃንን በቀኙ፥ ኃጢአተኞችን በግራው ያቆማቸዋል። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ! ተርቤ ነበር፥ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ ነበር፥ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ መጣሁ፤ በቤታችሁ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ ነበር፥ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ ነበር፥ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ነበር መጥታችሁ ጐብኝታችሁኛል።’ በዚያን ጊዜ ጻድቃን እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል፤ ‘ጌታ ሆይ፥ መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና በቤታችን ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና መጥተን ጠየቅንህ?’ ንጉሡም ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችኹት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው!’ ሲል ይመልስላቸዋል። ከዚህ በኋላ በግራው በኩል ያሉትንም እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ የተረገማችሁ! ከእኔ ወዲያ ራቁ! ለዲያብሎስና ለተከታዮቹ መላእክት ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ! ተርቤ ነበር አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ ነበር አላጠጣችሁኝም። እንግዳ ሆኜ መጥቼ ነበር፥ አልተቀበላችሁኝም፤ በቤታችሁ ታርዤ ነበር፥ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ ነበር፥ አልጠየቃችሁኝም፤’ እነርሱም ‘ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፥ እንግዳ ሆነህ ወይንም ታርዘህ፥ ታመህ ወይም ታስረህ መቼ አየንህና ሳንረዳህ ቀረን?’ ሲሉ ይመልሱለታል። ንጉሡም ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያላደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች