የማቴዎስ ወንጌል 25:20-40

የማቴዎስ ወንጌል 25:20-40 አማ05

አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ወደ ጌታው መጣና አምስት መክሊት አቅርቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ! ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም አደረግህ፤ አንተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። ሁለት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም ነው! አንተ ታማኝና መልካም አገልጋይ በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ቀርቦ፥ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንክበት የምትሰበስብ፥ ጨካኝ ሰው መሆንክን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁና ሄጄ ገንዘብህን በመሬት ውስጥ ቀበርኩት፤ ይኸውልህ ገንዘብህ!’ አለው። ጌታው ግን እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ! ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንኩበት እንደምሰበስብ የምታውቅ ከሆነ፥ ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስድ ነበር። በሉ ገንዘቡን ተቀበሉና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት። ላለው ሰው ሁሉ ይጨመርለታል ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ግን በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’ “የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ በክብር ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እርሱም ሕዝቦችን እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል። ጻድቃንን በቀኙ፥ ኃጢአተኞችን በግራው ያቆማቸዋል። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ! ተርቤ ነበር፥ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ ነበር፥ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ መጣሁ፤ በቤታችሁ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ ነበር፥ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ ነበር፥ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ነበር መጥታችሁ ጐብኝታችሁኛል።’ በዚያን ጊዜ ጻድቃን እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል፤ ‘ጌታ ሆይ፥ መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና በቤታችን ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና መጥተን ጠየቅንህ?’ ንጉሡም ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችኹት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው!’ ሲል ይመልስላቸዋል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች