የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 25:15-29

የማቴዎስ ወንጌል 25:15-29 አማ05

ጌትዮው ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በማካፈል፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት መክሊት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጠና ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለው ወዲያውኑ ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ። ሁለት መክሊት የተቀበለውም እንዲሁ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፈ። አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄደና መሬት ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። “ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ መጣና ከአገልጋዮቹ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ወደ ጌታው መጣና አምስት መክሊት አቅርቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ! ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም አደረግህ፤ አንተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። ሁለት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም ነው! አንተ ታማኝና መልካም አገልጋይ በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ቀርቦ፥ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንክበት የምትሰበስብ፥ ጨካኝ ሰው መሆንክን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁና ሄጄ ገንዘብህን በመሬት ውስጥ ቀበርኩት፤ ይኸውልህ ገንዘብህ!’ አለው። ጌታው ግን እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ! ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንኩበት እንደምሰበስብ የምታውቅ ከሆነ፥ ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስድ ነበር። በሉ ገንዘቡን ተቀበሉና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት። ላለው ሰው ሁሉ ይጨመርለታል ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች