የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 24:32-51

የማቴዎስ ወንጌል 24:32-51 አማ05

“የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ፥ ያ ጊዜ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህን ሁሉ ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዕወቁ። በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።” “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ዐይነት፥ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ዘመን፥ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያጋቡና ሲያጋቡ ነበር። የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከ ወሰዳቸው ድረስ አላወቁም ነበር፤ የሰው ልጅ አመጣጥም ልክ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ አብረው ይሠራሉ። አንደኛው ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች፤ ሌላይቱ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። እንዲሁም የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።” “ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ ማን ነው? ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ያን አገልጋይ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ አገልጋይ ግን፥ ‘ጌታዬ አሁን አይመጣም ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና የሥራ ጓደኞቹን መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ ያንን አገልጋይ ጌታው ይቀጣዋል፤ ዕጣ ክፍሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች