“በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ‘እነሆ፥ መሲሕ እዚህ አለ!’ ወይም ‘እዚያ አለ!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። “እንግዲህ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤ ታላቅ የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰሙ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ሄደው ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ያሉትን የእርሱን ምርጥ ሰዎች ይሰበስባሉ።” “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ፥ ያ ጊዜ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህን ሁሉ ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዕወቁ። በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።” “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ዐይነት፥ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ዘመን፥ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያጋቡና ሲያጋቡ ነበር። የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከ ወሰዳቸው ድረስ አላወቁም ነበር፤ የሰው ልጅ አመጣጥም ልክ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ አብረው ይሠራሉ። አንደኛው ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች፤ ሌላይቱ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። እንዲሁም የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።” “ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ ማን ነው? ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ያን አገልጋይ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ አገልጋይ ግን፥ ‘ጌታዬ አሁን አይመጣም ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና የሥራ ጓደኞቹን መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ ያንን አገልጋይ ጌታው ይቀጣዋል፤ ዕጣ ክፍሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
የማቴዎስ ወንጌል 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 24:23-51
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች