የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 21:1-19

የማቴዎስ ወንጌል 21:1-19 አማ05

ኢየሱስና ተከታዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በደብረ ዘይት ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደምትባለው መንደር ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ እዚያም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ወዲያውኑ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢላችሁ ‘ጌታ ስለሚፈልጋቸው ነው’ በሉት። እርሱም አህዮቹን ወዲያውኑ ይልካቸዋል።” ይህም የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦ “የጽዮን ከተማ ለምትባለው ለኢየሩሳሌም፦ ‘እነሆ! ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያይቱና በውርንጫዋ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል!’ ብላችሁ ንገሩአት።” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያዋንም ከነውርንጫዋ አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በአህዮቹ ጀርባ ላይ አደረጉ፤ ኢየሱስም በዚያ ላይ ተቀመጠ። ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስ ያደረገውን ድንቅ ነገር በማየታቸውና ሕፃናትም በቤተ መቅደስ “ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና! ምስጋና ይሁን!” እያሉ ሲጮኹ በመስማታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ኢየሱስን “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት፤ እርሱም “አዎ፥ እሰማለሁ፤ ‘ከልጆችና ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው፤ ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ቢታንያ ወደምትባል መንደር ሄደ፤ በዚያም ዐደረ። ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች