“መንግሥተ ሰማይ በወይኑ አትክልት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ጠዋት በማለዳ የወጣውን የአትክልት ባለቤት ትመስላለች። እርሱ ለእያንዳንዱ በቀን አንድ ዲናር ሊከፍል ተዋውሎ፥ ሠራተኞችን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ ላካቸው። በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ፥ ሥራ ፈተው በአደባባይ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አየ፤ ‘እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዳችሁ ሥሩ፤ የሚገባችሁንም ሒሳብ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። እነርሱም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዱ፤ ደግሞም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎች ሰዎች ቆመው አገኘና ‘እናንተስ ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ሰው አጥተን ነው’ አሉት፤ እርሱም ‘እንግዲያውስ፥ እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሂዱና ሥሩ’ አላቸው። “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሥራ ኀላፊውን ‘ሠራተኞቹን ጥራና በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በፊት እስከ ተቀጠሩት ድረስ የሥራ ዋጋቸውን ክፈላቸው’ አለው። ስለዚህ በዐሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ቀርበው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በፊት የተቀጠሩት በቀረቡ ጊዜ ይበልጥ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ገንዘቡን ተቀበሉና በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፤ ‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’ የወይኑ አትክልት ባለቤትም ከሠራተኞቹ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ወዳጄ ሆይ! ምንም አልበደልኩህም፤ የተዋዋልነው በቀን አንድ ዲናር ልከፍልህ አይደለምን? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያኽል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈቀድኩ። በገዛ ገንዘቤ የፈለግኹትን ማድረግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ለጋሥ ስለ ሆንኩ አንተ ትመቀኛለህ?’ ” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “እንዲሁም ኋለኞች የሆኑ ፊተኞች ፊተኞች የሆኑትም ኋለኞች ይሆናሉ፤” አለ።
የማቴዎስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 20:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች