የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 15:10-37

የማቴዎስ ወንጌል 15:10-37 አማ05

ቀጥሎም ኢየሱስ ሰዎቹን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! አስተውሉም! ሰውን የሚያረክሰው ከአፍ የሚወጣው ነው እንጂ ወደ አፍ የሚገባው አይደለም!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ፈሪሳውያን ይህን የተናገርከውን ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ዐውቀሃልን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል፤ እነርሱ ዕውሮችና ዕውሮችን የሚመሩ ስለ ሆኑ ተዉአቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።” ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን “የምሳሌውን ትርጒም አስረዳን” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተም እስከ አሁን ገና የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ወርዶ ወደ ውጪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውን የሚያረክሰውም እርሱ ነው። ክፉ ማሰብ፥ ሰው መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት ማድረግ፥ መስረቅ፥ በሐሰት መመስከር የሰውን ስም ማጥፋት፥ ይህ ሁሉ ከሰው ልብ ይወጣል። ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ ባልታጠበ እጅ መብላትስ አያረክሰውም።” ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች ሄደ፤ ከዚያም አንዲት ከነዓናዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ ትሠቃያለችና እባክህ ራራልኝ!” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ፤ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት!” ሲሉ ለመኑት። እርሱም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት እንደ በጎች ለጠፉት ብቻ ነው” ሲል መለሰ። ሴትዮዋ ግን ቀርባ በእግሩ ሥር ተንበረከከችና “ጌታ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ኢየሱስም “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል የተገባ አይደለም” አለ። እርስዋም “ጌታ ሆይ! እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ውሾችም ከጌቶቻቸው ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት እምነትሽ! ትልቅ ነው፤ ስለዚህ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ!” አላት። የሴትዮዋም ልጅ በዚያኑ ሰዓት ዳነች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራ ላይም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሰዎች አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ድዳዎችንና ሌሎችንም በሽተኞች ይዘው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ በእግሩም ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሳዎች በደኅና ሲራመዱ፥ ዕውሮች ሲያዩ በተመለከቱ ጊዜ ተደንቀው የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎቹ ከእኔ ጋር ሦስት ቀናቸው ስለ ሆነና የሚበሉት ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ ሲሄዱ በመንገድ ዝለው እንዳይወድቁ ምንም ሳይመገቡ ላሰናብታቸው አልፈቅድም።” ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ በዚህ በረሓ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች አሉን” አሉት። ከዚያ በኋላ፥ ኢየሱስ ሕዝቡ በመሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ደቀ መዛሙርቱ ሰብስበው ሰባት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች