ማቴዎስ 15:10-37
ማቴዎስ 15:10-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡንም ጠርቶ “ስሙ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፤ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን?” አሉት። እርሱ ግን መልሶ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ፤” አለ። ጴጥሮስም መልሶ “ምሳሌውን ተርጕምልን፤” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ “እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።” ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆም ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል፤” ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት፤” እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም፤” አለ። እርስዋ ግን መጥታ “ጌታ ሆይ! እርዳኝ፤” እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ “የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም፤” አለ። እርስዋም “አዎን ጌታ ሆይ! ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ፤” አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ድዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ በኢየሱስም እግር አጠገብ አስቀመጡአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ” አሉት። ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በሉና ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።
ማቴዎስ 15:10-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቡን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ፤ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም።” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ያልኸውን ሰምተው እንደ ተቈጡ ዐወቅህ?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፣ እነርሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውር መሪዎች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ተያይዘው ጕድጓድ ይገባሉ።” ጴጥሮስም፣ “ምሳሌውን አስረዳን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተም እስካሁን አይገባችሁምን? በአፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ዘልቆ፣ ከዚያም ወደ ውጭ እንደሚወጣ አታውቁምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይመነጫል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው፤ ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫሉና። ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን አያረክስም።” ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አካባቢ ወጥታ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ፤ ራራልኝ፤ ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “እየተከተለችን ትጮኻለችና ብታሰናብታትስ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ሆነው ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነው” አለ። ሴትዮዋም እግሩ ላይ ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፤ ርዳኝ” አለች። እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል አይገባም” አላት። እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከጌታቸው ማእድ የወዳደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ “አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው! እንደ ፈለግሽው ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለው ስፍራ በመሄድ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ። ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን ሕመምተኞች ይዘው ወደ እርሱ በማምጣት በእግሮቹ ሥር አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደኅና ሲሆን፣ ዐንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “ሕዝቡ ከእኔ ጋራ ሦስት ቀን ስለ ሆናቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው ለእነዚህ ሰዎች ዐዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ በራብ ዝለው እንዳይወድቁ ጦማቸውን ልሰድዳቸው አልፈቅድም” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “በዚህ ምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማብላት በቂ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ለመሆኑ ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትንንሽ ዓሣ” አሉት። እርሱም ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ።
ማቴዎስ 15:10-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡንም ጠርቶ፦ ስሙ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፦ ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት። እርሱ ግን መልሶ፦ የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ። ጴጥሮስም መልሶ፦ ምሳሌውን ተርጕምልን አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም። ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት። ኢየሱስም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት። ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።
ማቴዎስ 15:10-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ ሰዎቹን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! አስተውሉም! ሰውን የሚያረክሰው ከአፍ የሚወጣው ነው እንጂ ወደ አፍ የሚገባው አይደለም!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ፈሪሳውያን ይህን የተናገርከውን ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ዐውቀሃልን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል፤ እነርሱ ዕውሮችና ዕውሮችን የሚመሩ ስለ ሆኑ ተዉአቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።” ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን “የምሳሌውን ትርጒም አስረዳን” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተም እስከ አሁን ገና የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ወርዶ ወደ ውጪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውን የሚያረክሰውም እርሱ ነው። ክፉ ማሰብ፥ ሰው መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት ማድረግ፥ መስረቅ፥ በሐሰት መመስከር የሰውን ስም ማጥፋት፥ ይህ ሁሉ ከሰው ልብ ይወጣል። ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ ባልታጠበ እጅ መብላትስ አያረክሰውም።” ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች ሄደ፤ ከዚያም አንዲት ከነዓናዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ ትሠቃያለችና እባክህ ራራልኝ!” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ፤ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት!” ሲሉ ለመኑት። እርሱም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት እንደ በጎች ለጠፉት ብቻ ነው” ሲል መለሰ። ሴትዮዋ ግን ቀርባ በእግሩ ሥር ተንበረከከችና “ጌታ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ኢየሱስም “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል የተገባ አይደለም” አለ። እርስዋም “ጌታ ሆይ! እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ውሾችም ከጌቶቻቸው ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት እምነትሽ! ትልቅ ነው፤ ስለዚህ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ!” አላት። የሴትዮዋም ልጅ በዚያኑ ሰዓት ዳነች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራ ላይም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሰዎች አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ድዳዎችንና ሌሎችንም በሽተኞች ይዘው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ በእግሩም ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሳዎች በደኅና ሲራመዱ፥ ዕውሮች ሲያዩ በተመለከቱ ጊዜ ተደንቀው የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎቹ ከእኔ ጋር ሦስት ቀናቸው ስለ ሆነና የሚበሉት ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ ሲሄዱ በመንገድ ዝለው እንዳይወድቁ ምንም ሳይመገቡ ላሰናብታቸው አልፈቅድም።” ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ በዚህ በረሓ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች አሉን” አሉት። ከዚያ በኋላ፥ ኢየሱስ ሕዝቡ በመሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ደቀ መዛሙርቱ ሰብስበው ሰባት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።
ማቴዎስ 15:10-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው “ስሙ አስተውሉም፤ ወደ አፍ የሚገባው ሰውን አያረክሰውም፤ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ታውቃለህን?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ።” ጴጥሮስም መልሶ “ይህንን ምሳሌ ተርጉምልን” አለው። እርሱም “እናንተም እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ እነዚህ ሰውን ያረክሱታል። ከልብ ክፉ ሐሳብ፥ መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፥ ባልታጠበ እጅ መብላት ግን ሰውን አያረክሰውም።” ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር መጥታ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ ማረኝ፤ ሴት ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድ ቃልም አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ከኋላችን እየጮኸች ነውና አሰናብታት” እያሉ ለመኑት። እርሱም “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ነው እንጂ ለሌላ አይደለም” ሲል መለሰ። እርሷ ግን መጥታ እየሰገደች “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” አለች። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል መልካም አይደለም።” እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ! ነገር ግን ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” ሲል መለሰላት። ሴት ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ዲዳዎችን፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፥ በኢየሱስም እግር ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲፈወሱ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ፥ ምክንያቱም ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋል የሚበሉት ግን የላቸውም፤ በመንገድ ላይ እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልፈልግም” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “በዚህ በምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ የሚያጠግብ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት። ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣዎቹን ይዞ አመሰገነ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።