የማቴዎስ ወንጌል 13:18-35

የማቴዎስ ወንጌል 13:18-35 አማ05

“እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።” እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።” ኢየሱስ ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። እርስዋ ከዘር ሁሉ ያነሰች ናት ባደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፤ ዛፍም ትሆናለች፤ ወፎችም መጥተው በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይሰፍሩባታል።” ደግሞም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንዲት ሴት ወስዳ ከሦስት መስፈሪያ ዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፤ እርሾውም ሊጡን ሁሉ እንዲቦካ አደረገው።” ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች