በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም። የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ “የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም። “እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።” እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።” ኢየሱስ ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። እርስዋ ከዘር ሁሉ ያነሰች ናት ባደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፤ ዛፍም ትሆናለች፤ ወፎችም መጥተው በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይሰፍሩባታል።” ደግሞም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንዲት ሴት ወስዳ ከሦስት መስፈሪያ ዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፤ እርሾውም ሊጡን ሁሉ እንዲቦካ አደረገው።” ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ።
የማቴዎስ ወንጌል 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 13:1-53
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች