የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 10:1-25

የማቴዎስ ወንጌል 10:1-25 አማ05

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጡ፥ በሽታንና ደዌን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ዝርዝር፥ እንደሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ቶማስ፥ ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀናኢው ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። አንዱ አስተያየት፥ ከቦታ ወይም ከሀገር ጋር ሲያያይዘው ሌላው ወገን ደግሞ ይሁዳን ውሸታም ወይም አታላይ ብሎ ለመስደብ የተሰጠ ቅጽል ነው ይላል። ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ እንደ በጎች ወደ ጠፉት ወደ እስራኤል ሕዝቦች ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማይ ቀርባለች!’ እያላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በኪሳችሁ አትያዙ። ለሠራተኛ ምግቡ የሚገባው ስለ ሆነ ለመንገዳችሁ ከረጢት፥ ትርፍ እጀ ጠባብ፥ ትርፍ ጫማ፥ በትርም አትያዙ። በምትገቡበት ከተማ ወይም መንደር፥ ተገቢ የሆነ ሰው ማን እንደ ሆነ መርምሩ፤ ያንንም ስፍራ ለቃችሁ እስክትወጡ ድረስ ከእርሱ ጋር ቈዩ። ወደ ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱ ለሰላማችሁ ተገቢ ቢሆን ሰላማችሁ ይድረሰው፤ ተገቢ ባይሆን ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ማንም ሰው የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ቢሆን ያንን ቤት ወይም ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ሰዎች ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። “እነሆ! እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች፥ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ። ሰዎች ወደ ፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራባቸውም ይገርፉአችኋል፤ ስለዚህ ከሰዎች ተጠንቀቁ። በእኔ ምክንያት፥ ወደ ገዢዎችና ወደ ነገሥታት ለፍርድ ስለምትወሰዱ በእነርሱና በአሕዛብ ፊት ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤ ሰዎች ወደ ፍርድ ሸንጎ ሲያቀርቡአችሁ የምትናገሩት ነገር በዚያን ሰዓት ስለሚሰጣችሁ፥ ‘እንዴት ወይም ምን እንናገራለን?’ ብላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። በእናንተ ውስጥ ዐድሮ የሚናገር የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ሰው የገዛ ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ እንዲሁም አባት የገዛ ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ለሞትም አሳልፈው ይሰጡአቸዋል። በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻው ጸንቶ የሚቆም ይድናል። በአንድ ከተማ መከራ ሲያበዙባችሁ፥ ወደ ሌላው ሽሹ፤ በእውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞች ሁሉ አታዳርሱም። ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም። ስለዚህ ተማሪ እንደአስተማሪው፥ አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። የቤቱን ጌታ ‘ብዔልዜቡል’ ብለው ከጠሩት ቤተሰቦቹንማ ከዚህ በከፋ ስም እንዴት አይጠሩአቸውም!

ተዛማጅ ቪዲዮዎች