የሉቃስ ወንጌል 7:18-35

የሉቃስ ወንጌል 7:18-35 አማ05

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ እነዚህ ነገሮች ይህን ሁሉ ለእርሱ አወሩለት፤ እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ፥ “ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብላችሁ ጠይቁት፤” ሲል ወደ ጌታ ኢየሱስ ላካቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ሄደው “ ‘ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብላችሁ ጠይቁት ሲል መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል፥” አሉት። ኢየሱስ በዚያኑ ሰዓት ሰዎችን ከልዩ ልዩ በሽታና ደዌ ፈወሰ፤ ርኩሳን መናፍስትንም አስወጣ፤ የብዙ ዕውሮችን ዐይን አበራ። ኢየሱስ መልእክተኞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ተመልሳችሁ ሂዱና ለዮሐንስ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ንገሩት፤ እነሆ፥ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ቀጥ ብለው ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል። በእኔ የማይሰናከል የተባረከ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ እንዲህ እያለ ይናገር ጀመር፦ “ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን? ደግሞስ ምን ለማየት ወጣችሁ? የተዋበ ልብስ የለበሰውን ሰው ለማየት ነውን? የተዋበ ልብስ የሚለብሱና በድሎት የሚኖሩማ በነገሥታት ቤት ይገኛሉ፤ ታዲያስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ለማየት ነውን? አዎ፥ እላችኋለሁ፤ እንዲያውም ከነቢይ የሚበልጠውን ለማየት ነው። እርሱ ‘እነሆ! እፊት እፊትህ እየሄደ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥’ ተብሎ የተጻፈለት ነው። ሴቶች ከወለዱአቸው ሰዎች መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ይህን በሰሙ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቀራጮችም እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቀው ስለ ነበር የእግዚአብሔር ሥራ ትክክል መሆኑን ተገነዘቡ። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን በዮሐንስ እጅ አንጠመቅም በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተቃውመው ነበር። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? ምንስ ይመስላል? በአደባባይ ተቀምጠው የሚጫወቱ ልጆችን ይመስላል፤ እነርሱም እርስ በእርሳቸው እየተጠራሩ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ እናንተ ግን አላለቀሳችሁም፥’ የሚሉ ናቸው። እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅም ሳይጠጣ ቢመጣ ‘ጋኔን አለበት፤’ አላችሁት። የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፥ ‘እነሆ፥ ይህ መብልና መጠጥ የሚወድ ነው፤ የቀራጮችና የኃጢአተኞችም ወዳጅ ነው፥’ አላችሁት። የጥበብ ትክክለኛነት በልጆችዋ ይረጋገጣል።”