የሉቃስ ወንጌል 6:6-16

የሉቃስ ወንጌል 6:6-16 አማ05

በሌላም ሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ እዚያም ቀኝ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ወንጀል ለማግኘት ፈልገው፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጀ ሽባውን “ተነሥና በመካከል ቁም!” አለው፤ ሽባውም ተነሣና በመካከል ቆመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን? ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ኢየሱስ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እጀ ሽባውን፥ “እጅህን ዘርጋ!” አለው። እርሱም እጁን በዘረጋው ጊዜ ዳነለትና እንደ ሌላው እጅ ደኅና ሆነ። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን በጣም ተቈጥተው በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። አንድ ቀን ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፤ እዚያ ሌሊቱን ሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእነርሱም መካከል ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና “ቀናተኛ” ተብሎ የሚጠራው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮታዊው ይሁዳ።