ሉቃስ 6:6-16

ሉቃስ 6:6-16 NASV

በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከስሱት ምክንያት በመፈለግ፣ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለችበትን ሰው፣ “ተነሥተህ መካከል ላይ ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም፣ “እስኪ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን በቍጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ። ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስም ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጥቶ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀነናዊው የተባለው ስምዖን፣ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።