የሉቃስ ወንጌል 6:27-49

የሉቃስ ወንጌል 6:27-49 አማ05

“ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም ነገር አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው፤ አንዱን ጒንጭህን በጥፊ ለሚመታህ፥ ሌላውንም ጒንጭህን እንዲመታ አዙርለት፤ ነጠላህን ለሚወስድብህ፥ እጀ ጠባብህንም ጨምረህ ስጠው፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም የሚወዱአቸውን ይወዳሉ፤ መልካም ነገር ለሚያደርጉላችሁ እናንተም መልካም ነገር ብታደርጉላቸው ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ ‘ይመልሱልናል’ ብላችሁ ለምታስቡአቸው ሰዎች ብታበድሩ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ? ያንኑ ያበደሩትን መልሰው ለመቀበልማ ኃጢአተኞችም ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ! መልካም ነገርም አድርጉላቸው፤ ‘ብድራችን ይመለስልናል’ ብላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ይህን ብታደርጉ ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጆችም ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለውለታ ቢሶችና ለክፉዎች እንኳ ሳይቀር ቸር ነው። የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሓሪዎች ሁኑ። “በማንም ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትንቀፉ፤ እናንተም አትነቀፉም፤ ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅርታ ታገኛላችሁ፤ ስጡ፤ ለእናንተም ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ እንዲሁ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም በጥሩ መስፈሪያ ታምቆና ተጠቅጥቆ እስኪትረፈረፍ ድረስ ተሰፍሮ ይሰጣችኋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? እንዲህማ ቢያደርግ ሁለቱም ተያይዘው በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ ይሁን እንጂ ተማሪ ትምህርቱን በደንብ ከተማረ እንደ አስተማሪው ይሆናል። “በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ስለምን በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? ደግሞስ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ወንድሜ ሆይ፥ እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ፤’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ። “መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ አያፈራም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ እንዲሁም ከእሾኻማ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ አይለቀምም። ስለዚህ ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካምን ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከመጥፎ ልቡ ክፉውን ነገር ያወጣል። ሰው በአፉ የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “እኔ የምነግራችሁን አትፈጽሙም፤ ታዲያ፥ ስለምን ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እያላችሁ ትጠሩኛላችሁ? ወደ እኔ የሚመጣና ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ማንን እንደሚመስል ልንገራችሁ፤ እርሱ በጥልቅ ቆፍሮ ቤቱን በጽኑ አለት ላይ የመሠረተውን ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በጽኑ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ ሊያነቃንቀው አልቻለም። ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ያለ መሠረት ቤቱን በዐፈር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት በገፋው ጊዜ ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም እጅግ ታላቅ ሆነ።”