የሉቃስ ወንጌል 5:33-39

የሉቃስ ወንጌል 5:33-39 አማ05

አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን፦ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ብዙ ጊዜ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉም፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ሁልጊዜ የሚበሉትና የሚጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች መጾም ይገባቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፥ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “የአዲስ ልብስ ዕራፊ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህን ቢያደርግ ግን አዲሱን ልብስ ይቀደዋል፤ አዲሱም ዕራፊ ለአሮጌው ልብስ አይስማማም፤ እንዲሁም በአረጀ የወይን ጠጅ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ስለዚህ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፤ ብዙ ጊዜ የቈየ ደረቅ የወይን ጠጅ የጠጣ አዲሱን በተሐ የወይን ጠጅ መጠጣት አይፈልግም፤ ‘የቈየው ደረቅ የወይን ጠጅ የተሻለ ነው፥’ ይላልና።”