የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 3:1-22

የሉቃስ ወንጌል 3:1-22 አማ05

የሮም ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጰንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ምድር አስተዳዳሪ ነበር፤ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዢ ነበር፤ እንዲሁም ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሌኔ ገዢ ነበሩ፤ ሐናና ቀያፋም የካህናት አለቆች ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ በበረሓ ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ስለዚህ ዮሐንስ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ እየተዘዋወረ፦ “ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ፤” እያለ ያስተምር ነበር። ይህም የሆነው፦ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ አስቀድሞ እንዲህ ሲል በጻፈው መሠረት ነው፦ “እነሆ! ይህ በበረሓ እንዲህ እያለ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነው፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ! ጥርጊያውንም አቅኑ! ጐድጓዳው ቦታ ሁሉ ይደልደል! ተራራና ኰረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል! ጠማማው መንገድ ይቅና! ሻካራውም መንገድ ይስተካከል! ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ!’ ” ሊጠመቁ ወደ እርሱ የመጡትን ብዙ ሕዝብ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የመርዘኛ እባብ ልጆች! ከሚመጣው ከእግዚአብሔር ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ? ይልቁንስ ንስሓ መግባታችሁን የሚያመለክት ሥራ ሥሩ እንጂ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን እያላችሁ በልባችሁ አትመኩ። እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እንደሚችል እነግራችኋለሁ። አሁን መጥረቢያ በዛፎቹ ሥር ተቀምጦአል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም “ታዲያ፥ ምን እናድርግ?” ሲሉ ዮሐንስን ጠየቁት። እርሱም፦ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ፤ ምግብ ያለውም ለሌለው ያካፍል፤” አላቸው። ቀራጮችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው “መምህር ሆይ! እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ “በሕግ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትጠይቁ፤” አላቸው። ወታደሮችም መጥተው፥ “እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት፤ እርሱም፦ “የሰው ገንዘብ በግፍ ነጥቃችሁ አትውሰዱ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ የራሳችሁ ደመወዝ ይብቃችሁ፤” አላቸው። በዚያን ዘመን ሕዝቡ ሁሉ የመሲሕን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ ስለዚህ ዮሐንስን “ይህ ሰው ምናልባት መሲሕ ይሆንን?” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ዮሐንስ ግን ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ሌላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ የእርሱን ጫማ ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። እርሱ በአውድማ ላይ እህሉን ከገለባ ለመለየት መንሹን በእጁ ይዞአል፤ ካጣራውም በኋላ ጥሩውን እህል በጐተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” እንዲሁም ዮሐንስ በልዩ ልዩ መንገድ ሕዝቡን እየመከረ መልካሙን ዜና ያበሥር ነበር። የገሊላውን ገዢ ሄሮድስን ግን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱና ሌላም ብዙ ክፉ ነገር በማድረጉ ገሠጸው። ሄሮድስ በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወደ ወህኒ ቤት አስገባው። ሰዎች ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እርሱ ሲጸልይ ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ወረደ፤ በዚያኑ ጊዜ “አንተ የተወደድክ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።