ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤ ይኸውም፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤ “በምድረ በዳ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አቅኑ፤ ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው መንገድ ቀና፣ ወጣ ገባውም ጐዳና ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል፤ የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ” ዮሐንስም በርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባት አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና። እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው። ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት። እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው። ወታደሮች ደግሞ፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” አላቸው። ሕዝቡ በጕጕት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር። ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታው ይመጣል፤ እኔም የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ዮሐንስም በብዙ ሌሎች የምክር ቃላት ሕዝቡን እያስጠነቀቀ ወንጌልን ሰበከላቸው። ነገር ግን ዮሐንስ፣ የአራተኛውን ክፍል ገዥ ሄሮድስን የወንድሙ ሚስት በነበረችው በሄሮድያዳ ምክንያትና ስለ ሌሎች ሥራዎቹ በገሠጸው ጊዜ፣ ሄሮድስ ይህን በሌላው ሁሉ ላይ በመጨመር፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው። ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በአካላዊ ቅርጽ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም፣ “የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ መጣ።
ሉቃስ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 3
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 3:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos