የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 24:13-27

የሉቃስ ወንጌል 24:13-27 አማ05

በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ተከታዮች ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያኽል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ተብላ ወደምትጠራ መንደር ይጓዙ ነበር። እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር ሁሉ አንሥተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። ይህንንም በሚያወሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር። ነገር ግን በዐይናቸው እያዩት ማን እንደ ሆነ ማወቅ አልቻሉም። እርሱም “በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እያዘኑ ቀጥ ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው።