ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት። ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። ስለዚህም ነገር በመገረም ላይ ሳሉ እነሆ፥ የሚያንጸባርቅ ብሩህ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች መጥተው በአጠገባቸው ቆሙ። ሴቶቹም እጅግ ፈርተው ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ ሰዎቹ፦ “ስለምን ሕያውን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? አሉአቸው። እርሱ እዚህ የለም፤ ተነሥቶአል፤ በገሊላ በነበረበት ጊዜ የነገራችሁን አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች ተላልፎ መሰጠት፥ መሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ከሞት መነሣት ይገባዋል’ ብሎአችሁ ነበር።” ሴቶቹም የኢየሱስን ቃል አስታወሱ፤ ከመቃብርም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለቀሩትም ነገሩአቸው። ይህን ለሐዋርያት የተናገሩት መግደላዊት ማርያም፥ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም፥ እንዲሁም ሌሎች ሴቶች ነበሩ። እነርሱ ግን ይህ ነገር ቅዠት ስለ መሰላቸው አላመኑአቸውም። ነገር ግን ጴጥሮስ ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያም ሲደርስ ጐንበስ ብሎ በተመለከተ ጊዜ አስከሬኑ የተከፈነበትን ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀመጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤት ተመለሰ። በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ተከታዮች ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያኽል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ተብላ ወደምትጠራ መንደር ይጓዙ ነበር። እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር ሁሉ አንሥተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። ይህንንም በሚያወሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር። ነገር ግን በዐይናቸው እያዩት ማን እንደ ሆነ ማወቅ አልቻሉም። እርሱም “በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እያዘኑ ቀጥ ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው። እነርሱ ወደሚሄዱበት መንደር በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “ቀኑ መሽቶአል፤ ፀሐይም መጥለቅዋ ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር እዚህ ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር ሊያድር ወደ ቤት ገባ። ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ እንጀራ አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ቈርሶ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተና ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ ግን ወዲያው ከዐይናቸው ተሰወረ። እነርሱም እርስ በርሳቸው “በመንገድ ሳለን ሲነግረንና ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየጠቀሰ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?” ተባባሉ። እነርሱም በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ፤ በዚያም ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርት አብረዋቸው ካሉት ጋር በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል!” ይሉ ነበር። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ጌታ ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁትም ተረኩላቸው።
የሉቃስ ወንጌል 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 24:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች